
መሰረታዊ እውነቶች እና የእምነታችን አቋማችን
የመንፈሳዊ ህይወት ጉዞ ጅማሬ ክርስቶስ እየሱስን እንደግል አዳኝ አድርጎ በመቀበል ሲሆን፥ ኢየሱስን እንደግል አዳኝ አድርጎ መቀበል በህይወታችን እግዚአብሄር ላለው አላማ እና የዘለአም ህይወትን ለመጨበጥ በር ከፋች ነው። መዳንን ለመቀበል እምነት የመጀመርያው እና ዋናው አስፈላጊ ጉዳይ ሲሆን ለማመን ውሳኔያችን ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
የደህንነት መሰረታዊ እውነታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው።
ደህንነት አዳም እና ሄዋን ይኖሩበት ከነበረው መጽሀፍ ቅዱስ ገነት ብሎ ከጠራው አለም ውስጥ እግዚአብሄር በአምሳሉ ከፈጠረው ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የመስራት ሙሉ ግንኙነት እና ህብረት እንዲኖረው የሚያስችለውን እግዚአብሄር ለአዳም የሰጠውን ትእዛዝ የሰው ልጅ (አዳም) ባለመታዘዝ ምክንያት ባመጣው ውድቀት እና መለያየት እግዚአብሄር እንደገና ግንኙነቱን ከሰው ልጅ ጋር ለማደስ የተጠቀመበት መንገዱ ነው። ዘፍ1 3 ትን ያንብቡ። ምንም እንኳን አዳም የአለመታዘዙ ውጤት ሞትን እንድሚያስከትል ቢነገረውም (ዘፍ1፥15_17) እግዚአብሄርን ባለመታዘዝ ሞትን ወደ ህይወቱ እንደጋበዘ እና በዚህም አለመታዘዝ ሞት እንደ ሰንስንለት ወደ እርሱ እና ወደ ወለዳቸው ልጆች ስልጣን አግኝቶ ከዛም ወደ ሰው ልጆች ሁሉ ሲተላለፍ እንመለከታለን። '' ሮሜ5፥12 ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ ''
ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው
ስለዚህ ፍቅር የሆነው እግዚአብሄር የሰውን ልጅ እንዲሁ ያለ ተስፋ አልተወውም ይልቁንም እንደገና ለመዋጀት እቅድን ማዘጋጀት አስፈለገው።ይህንንም ድርጊቱን የደህንነት መንገድ ብለን እንጠራዋለን።
የደህንነት መንገድ የሰው ልጅ የተሸነፈበትን ሀጥያትን እና ሞትን በማሸነፍ እግዚአብሄር ሰውን ለራሱ ክብር መልሶ ለማቅረብ የሄደበት መንገዱ ሲሆን በዚህም ድርጊቱ የስውን ልጅ ከእርሱ ጋር እንዲለያይ ያደረገውን የሀጥያት ደሞዝ የሆነውን የሞትን ዋጋ በመክፈል የሰው ልጅ የሀጥያት ይቅርታን እንዲያገኝ በማድረግ እግዚአብሄር የሰውን ልጅ ከራሱ ጋር ያስታረቀበት ትልቅ ጥበቡ ነው። ይህ ድርጊት በሰው ፈጽሞ የማይቻል በመሆኑ እግዚአብሄር አንድ ልጁን በመላክ መፈጸሙ እግዚአብሄር ለሰው ልጅ ያለውን ትልቅ ፍቅሩን ያስረዳናል። ዮሀ 3፥16-17
እንዲሁም ይህ ድርጊቱ ከኛ ጥረት እና ችሎታ ሳይሆን በእግዚአብሄር ምህረት እና ችሎታ እንደተደረገልን እና እኛም ከጸጋው የተነሳ ኢየሱስ የከፈለውን ዋጋ በማመን እና እርሱን እንደግል አዳኛችን አድርገን በማመን ብቻ የሚገኝ መዳን እንደሆነ መጽሀፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳናል። ሮሜ5፥7 11
''ሮሜ 10፥9 ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ 10 ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና''
መጽሀፍ ቅዱስ የእግዚአብሄር ቃል ነው።
መጽሀፍ ቅዱስ በእግዚአብሄር ዘንድ የነበረ፥ የአሁን እና የሚመጣውን የእግዚአብሄርን የራሱን ፍላጎት እና እቅድ ለሰው ልጅ (ለግላችን ለቤተሰባችን ለቤተክርስቲያናችን እና ለምድር) በዘመናት ውስጥ የገለጠበት እና እየገለጠበት ያለበት በመንፈስ የተጻፈ መጽሀፍ ነው።''2ጢሞ3፥16 የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል''
የመጽሀፍ ቅዱስ አንዱ ዋና እና አስገራሚ የሆነው ባህርይ ምንም እንኳን ለመጻፍ 40 በሚሆኑ በተለያዩ ጸሀፊዎች ከ1800 አመታት በላይ በወሰደ ግዜ ቢጻፍም ፈጽሞ እርስ በእርሱ የማይጋጭ መሆኑ ነው። መጽሀፍ ቅዱስ አዲስ ኪዳ እና ብሉይ ኪዳን በመባል በሁለት የተከፈለ መጽሀፍ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሄር ከሰው ልጆች ጋር የነበረውን ግንኙነት የያዘውን 39 መጽሀፍት ብሉይ ኪዳን ብለን ስንጠራው ኢየሱስ ወደዚህ ምድር ከመጣ እና ካረገ በህዋላ ያለውን 27 መጽሀፍ ደግሞ አዲስ ኪዳን በማለት እንጠራዋለን።ይህም በአጠቃላይ 66 መጽሀፍት የያዘ መሆኑን ያስረዳናል።
መጽሀፍ ቅዱስ ከሚታወቅበት ባህሪዎቹ ጥቂቶቹ እግዚአብሄር እራሱ በስልጣን እኔ በማለት የሚናገርበት፥ባህሪውን የገለጸበት፥ለሰው ልጅ ያለውን አላማ፥ቃል ኪዳኑን እና ተስፋውን የገለጠበት መጽሀፍ በመሆን ነው። እንዲሁም በውስጡ ታሪኮችን፥ፍልስፍናን፥ቅኔዎችን እና ትንቢቶችን የያዘ መጽሀፍ ነው።
የጥምቀት አስፈላጊነት
የውሃ ጥምቀት ለእግዚአብሄር የመታዘዛችን ምልክት ሲሆን በአንድ አማኝ ህይወት ውስጥ ትክክለኛ የውስጥ ለውጥ መካሄዱን ለመግለጥ የምንተገብረው ድርጊት ነው። ይህም ኢየሱስ በምድር ላይ በምሳሌነት የተመላለሰበትን የህይወት ልክ ለመኖር ያለንን ውሳኔና ቁርጠኝነት ያሳያል
''ሮሜ6፥4 እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። 5ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤6 ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና።''
የጥምቀትን አስፈላጊነት ኢየሱስ እራሱ በመጠመቅ ያሳየን ሲሆን ይህንን አለም ለቆ ከመሄዱ በፊት ሁሉም ሰው እርሱን እንደግል አዳኝ አድርጎ ካመነ በሗላ ይህንን ስርአት እንዲያደርጉ ትእዛዝ መስጠቱ ይህ ስርአት ትልቅ የሆነ መንፈሳዊ ክብደት ያለውና በአማኞች ለተገበር የሚገባ መሆኑን አመልካች ነው።
የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት
አማኞች የእግዚአብሄርን ስራ በትጋት እንዲሰሩ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አስፈላጊ እንደሆነ መጽሀፍ ቅዱሳችን በተለያየ ቦታዎች ይገልጽልናል። በተለይ በሀዋርያት ስራ ምእራፍ 1 ቁጥር 8 ላይ ኢየሱስ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።በማለት ይህ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በህይወታቸው ላይ ለአገልግሎታቸው ትልቅ ጉልበትን እንደሚሰጣቸው ገልጦላቸው ነበር። ይህም ሂደት ከዚያ በህዋላ ባላቸው እንቅስቃሴ በልጽ የታየ ሲሆን የመንፈስ ቅዱስን ሀይል መቀበላቸው ቃሉን በትልቅ መረዳት በግልጽነት እንዲናገሩ እና በድፍረት ለሌሎች እንዲመሰክሩ አስችሎአቸዋል።
እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ለአማኞች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ለመቀበል በር ከፋች ሲሆን እነዚህ ስጦታዎች እግዚአብሄር ቤተክርስቲያንን ወደሙላት ለማምጣት እና ለማነጽ የሚጠቀምባቸው መሆኑን በመረዳት አማኞች ልንጠማቸው እና ከተቀበልን በሗላ ደግሞ አካሉ በሆነችው በቤተክርስቲያን ውስጥ በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ይገባል።በተለይ አሁን በገባንበት በዘመን መጨረሻ በኤፌሶን ምእራፍ 4፥11 ላይ የተገጡት ስጦታዎችን ቤተክርስቲያን ልዩ ትኩረትን በመስጠት አካሉን ለፍጽምና ልታዘጋጅ ይገባታል።
''ኤፌ411እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ 12-ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።''
የቤተክርስቲያን ( ማህበረሰብ) አስፈላጊነት
ቤተክርስቲያን የእግዚአብሄር የዘለአለም ሀሳቡ ስትሆን ቤተክርስቲያን ህንጻው ሳይሆን በእግዚአብሄር ልብ ውስጥ ያለውን የዘለአለም ሀሳብ ወደ ፍጻሜ ለማምጣት በህይወት የለውጥ ግንባታ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ እና ትንቢታዊውን የእግዚአብሄር ሀሳብ ወደ ሙላት ለማምጣት የተጠሩ ሰዎች ስብስብ ነች ማቴ16፥17 ኢየሱስም •••ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። እዚህ ቦታ ቤተክርስቲያን የሚለው የግሪኩ ቃል “ekklesia” ለአንድ አላማ የተጠሩ እንደማለት ሲሆን ይህም ቤተክርስቲያን በብዙ አቅጣጫ የህይወት ተሳትፎ ያለበት የግንባታ ህይወት ስብስብ እንጂ ሀይማኖታዊ ተቋም እንዳልሆነ ያስረዳናል።
ስለዚህ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሄርን ፍላጎት በበለጠ ለማሟላት እንድንችል እግዚአብሄር ማህበረሰብን ፈጥሮልናል ማለት እንችላለን ይህም በህብረት የምናደርገው አንድ ግብ ላይ ያተኮረ የአንድነት እንቅስቃሴ ብዙ ፌሬ እንድናፈራ እና በቀላሉ ትልልቅ ድሎችን እንድንጨብጥ ያስችለናል።
''ሌዋ 26 ፥ 8 “ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም አሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።'' ይህ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል የሚያሳየን አንደ ግለሰብ ከማህበረሰቡ ጋር በአንድ ዓይነት ዓላማ ስንወሃድ ተዓምራታዊ በሆነ መንገድ ምርታማነት (ፌሬያማነት) እንደሚጨምር ነው፣
ስለዚህ የአንደ ግለሰብ የምናደርገው እንቅስቃሴ ዓላማ ሁሉ ለበማህበረሰቡ ዕድገት ሊሆን ይገባል ማለት ነው። እንዲሁም ይህ እውነታ እኔ በግሌ የማደርገው እንቅስቃሴ ጠቃሚነቱ ለመላው አካሌ (ለማህበረሰቡ) አስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ሊሆን ይገባል ወደሚል አመለካከት ይወስደናል።
''ማቴ 18:19 “ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። 20ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።''
ከላይ እንደተመለከትነው የዚህ ዓይነት ህበረት መኖራችን እግዚአብሄር ስለእኛ ሆኖ እቅዱን ሊያንቀሳቀስ እንደሚያስችለው በግልጽ ያስረዳናል። እንዲሁም በዚህ ስፍራ መስማማት (Agree)-የሚለውን ቃል በእንግሊዘኛው ትርጉም Symphony (ሲምፖኒይ) ማለት አንድን ውጤት ለማምጣት በጋራ የሚደረግ የእያንዳንዱ የግል እንቅስቃሴ ማለት ሲሆን ፣በአንድ አላማ ላይ ያተኮረ እንደዚህ አይነት ህብረት ኖሮ መስራት በጋራ ለምናደርገው እርምጃ ከተፈጥሮአዊው ግምት በላይ የሆነ ጥንካሬን፥ልዩ ችሎታን እና አስደናቂ ውጤትን እንደሚሰጠን የሚያስረዳ ክፍል ነው።
የተሀድሶ አስፈላጊነት
ተሃድሶ የሚለውን ቃል በግልጽ በመጸሃፍ ቅዱሳችን የምናገኝበት አንዱ ቦታ ቢኖር በ እብ9፣8-10ላይ ሲሆን እግዚአብሄር ወደዘለአለም ሀሳቡ ሲገሰግስ በጉዞ ውስጥ ደረጃ በደረጃ እራሱን እና ሀሳቡን የሚገልጥበት የሰማያዊ እውነት ሂደት እንደሆነ መጽሀፍ ቅዱሳችንም ሆነ ታሪክ ያስረዳናል።
'' እብ9፣8-10 ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው(ኣዲሱ) መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።9-10ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፥ እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ፤ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም።'' እንዲሁም በሐዋ3.21''እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና።በማለት ክርስቶስ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ የተሀድሶን ቀጣይነት ያሳየናል።''
ተሃድሶ የሚለው ቃል በግሪክ diorthosis (ዲዮርቶሲስ) ማለት ሲሆን ትርጉሙአንድን ነገር በቀጣይነት ማቃናት እንዲሁም አንድን ነገር ወደ ቀደመው የትፈጥሮ እና ትክክለኛ ቦታው በመመለስ ቀጥ የማድረግ ሁኔታ ወይንም ቦታውን የለቀቀ፣ የተሰበረ ወይንም የተጣመመ አጥንትን ወደ ቦታው የመመለስ ሂደትን ያሳያል በእንግሊዝኛው ኦርቶፔዲክ የሚለውን ቃል ሲይዝ ቃሉን ለህክምና ባለሞያዎች አጥንትን እና ጡንቻን ለማቃናት በሚደረገው የጥናት ክፍል ይጠቀሙበታል Ortho-paideia የሚለው አግሪክ ቃል የሁለት ቃል ጥምር ሲሆን ኦርቶ- ማቃናት ሲሆን- ፒያዲያ ደግሞ ህጻናትን ሙሉ ለሙለ እስከሚያድጉ መንከባከብን ያሳያል። ስለዚህ ተሃድሶ የደህነት ሙላት ዋናው ክፍል ነው ማለት እንችላለን።
ደህንነት በተሀድሶ ቋንቋ ህይወትን ማካፈል፥በአንድነት ጌታን ማምለክ፥በሁሉም አቅጣጫ ለህይወት መለኮታዊ ምሪትን መቀበል፥በሁሉም የህይወት አቅጣጫ የሚደረግ የነጻነት ጉዞ ፥ጸጋን መካፈል ማለት ሲሆን አማኞች ወደዚህ የብስለት ሙላት እንዲመጡ ተሃድሶ በጣም አስፈላጊ እና ቁልፍ እውነት ነው። ተሀድሶ ከግል ሂደት አልፎ በማህበር ሲተረጎም የፊት መጨማደድ የሌለባትን ውብ የሆነችን ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ ለማቅረብ ትልቅን ሚና የሚጫወት ሲሆን በውጤቱም ቤተክርስቲያን ይህን ቁሳቁስ የሞላበትን አለማዊ አመለካከት እና ቀስ በቀስ ወደ ቤተክርስቲያን ጠላት ያስገባውን ፍልስፍና በማሸነፍ በምትኩ ቤተክርስቲያን በኢሳ60፥1 እና 2 ላይ የተገባላትን ቃል ተፈጻሚነትን እንዲያገኝ ትልቅ ሚናን ይጫወታል። '' ኢሳ60፥1ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ። 2 እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ ፤3 አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።''